1
    HEBREZEMA.INFO
    INDEPENDENT NEWS & MEDIA
    DESIGNED BY ZEWDU TEKLU
    © COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED 2007.
admin@hebrezema.info
1

በአውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በ1895 ዓም በዌል ሳንድ በተጻፈው ሳይንሳዊ ልብወለድ መነሻነት የተሰራው
ታይም ማሽን የተሰኘውን ፊልም ደጋግሜ አይቸዋለሁ፡፡

እንደ ጋይ ፒርስ ፣ጀርሚ አይረን ፣ኦርላንዶ ጆንስና ሳማንታ ሙምባ የመሳሰሉ ታዋቂ ተዋንያን የሚተውንበት ይህ
ፊልም ወደ አለፈ ጊዜ የኋልዮሽ በሚወስድ መንኮራኩር እየተጓዙ ያለፈውን ጊዜ የሚመለከቱበት ነው፡፡

ፊልሙን ባየሁት ቁጥር እንደው እውነት በሆነና ይህን የጊዜ ማሽን ማግኘት ብችል ወደ ኋላ ተጉዤ በርካታ
የህይወቴ ምስቅልቅሎችን ማስተካከል በቻልኩ ስል ተመኝቻለሁ፡፡

ይታያችሁ ይህ ማሽን ቢኖረኝ አለም ስትፈጠር ወደነበረችበት ጊዜ ተጉዤ ምን እንደምትመስል ማየትና ድሮና
ዘንድሮን ማነጻጸር ብችል የሚሰጠኝን ደስታ ሳስበው ፊልሙ እውነት በሆነ ያሰኘኛል፡፡

በአካል የማላውቃቸውን እነሉሲን ፣ ድንጋይን በድንጋይ ቆርጠውና ጠርበው የአክሱምን ሀውልትና የላሊበላን ውቅር
አብያተ ክርስትያናትን ያነጹ ጥበበኞችን ፣ ጀግኖች ነገስታትንና አያት ቅድመ አያቶቼን ምን እንደሚመስሉ ማየት
የሚሰጠኝን እርካታ ሳስበው ሀሴት ተሰማኝ፡፡

ውይይይይ….. ህልም እልም እንዳትሉኝ ይሄስ ህልም አይሁን ያሰኛል፡፡

ይህን እንዳስብ ያደረጉኝ ለረጅም አመታት በታሪክ  መምህርነት ያገለገሉት አቶ አይነኩሉ ጎሀጽባህ ናቸው፡፡

ከዛሬ 63 ዓመት በፊት በአውሮፓ ተካሂዶ ስለነበር አንድ ስብሰባ ሲያወጉኝ ሳይንሳዊ ይዘት ያለው የጊዜ ማሽን
ፊልም ትውስ አለኝ፡፡

በአቶ አይነኩሉ ትረካ የጊዜ መንኮራኩርነት ተሳፍሬ የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ስብሰባን ለመካፈል የኋልዮሽ ተጓዝኩ፡፡
መነሻዬ በአውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በ2016 ዓ.ም ኢትዮጵያ - መድረሻዬ ከ63 ዓመት በኋላ በ1953 ዓ.
ም እንግሊዝ ለንደን በየሃሊዮሽ ጉዞ አቆጣጠር ፡፡

በብርሃን ፍጥነት የሚጓዘው የጊዜ መንኮራኩር ስብሰባው በሚካሄድበት የእንግሊዟ ርዕሰ መዲና ከሆነችው ለንደን
ሰማይ ላይ እየተንሳፈፍኩ ለስብሰባው የሚደረገውን ሽርጉድ አስቃኘኝ፡፡

የለንደን ከተማ የአፍሪካና የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ የሆኑ የካሪቢያን ሀገራት ታላላቅ መሪዎችና ደጋፊዎች
የሚሳተፉበትን ስብሰባ ለማስተናገድ ተፍተፏን ተያይዛዋለች፡፡

የወቅቱ ዘመናዊ አውቶሞቢሎች በስብሰባው ለመታደም የመጡ የአፍሪካ መሪዎችን በዲፕሎማቲክ ደንብ አጅበው ጆሮ
የሚያደነቁር ጡሩምባቸውን እያሰሙ ስብሰባው ወደ ሚካሄድበት አዳራሽ ይፈተለካሉ፡፡

በለንደን እንብርት የእንግሊዝን ልዕልቶችና ልዑላን ጭነው በሰጋር ፈረሶች የሚጎተቱት ጋሪዎች አጥንት ላይ የሰፈረ
የጉንዳን ሰራዊት ይመስል ይተራመሳሉ፡፡

በከተማዋ ሽር ጉድ እየተደመምኩ የምልሰት ጉዞዬ መዳረሻ በሆነውና ታላቁ ስብሰባ በሚካሄድበት አዳራሽ ውሰጥ
ተከሰትኩ፡፡


ስብሰባው ምቹና የማይሰለች እንዲሆንና አዳራሹን ውበት ለማላበስ የውስጥ ግድግዳው ከዳር እስከዳር ቀለማቱ
በፈጠሩት ህብር ልብን ውክክ በሚያደርግ አላማ አሸብርቋል፡፡

በአዳራሹ አራቱም ማዕዘናት በቆሙ ቄንጠኛ ረጃጅም ሰንደቆች ላይ ይኸው ዓላማ ተሰቅሏል፡፡
የፓን አፍሪካኒዝምን መሰረት የጣሉት የጋናው የነጻነት ንቅናቄ መሪ ክዋሚ ንክሩማህ ፣ የማኡ ማኡ ንቅናቄ መሪ
ጆሞ ኬንያታ ፣ የአይቮሪኮስቱ ሀፋዊ ሽዋኝ ፣ የማሊው ሀንግስተን ባንዳ በልዩ አለባበስ  ደምቀው ወደ አዳራሹ ገቡ፡፡

ጆሞ ኬንያታ በጭንቅላታቸው ላይ እንደሻሽ የጠመጠሙት ክዋሚ ንክሩማህ በሙሉ አካላቸው ላይ  በልዩ ሁኔታ
የጠቀለሉት አዳራሹን ያስዋበውና በቀለማት ህብር የደመቀውን አላማ ነው፡፡

የደቡብ አፍሪካና ጎፈር በራሳቸው ላይ የደፉ የጃማይካ ነጻነት ታጋዮች በእጃቸው ይህን አላማ ይዘው ወደ አዳራሹ
በመግባት ስፍራቸውን ያዙ፡፡

ዙሪያ ግድግዳውን ሸፍነውና በአራቱም ማዕዘናት ባማረ ሰንደቅ ላይ ተሰቅለው በቀለማቸው ህብር አዳራሹን ያደመቁት፤
በጆሞ ኬንያታ ጭንቅላት ላይ እንደሻሽ ተጠምጥሞ ውበትን ያጎናጸፏቸው፣  ክዋሚ ንክሩማህን  በሙሉ አካላቸው
ላይ ተጠቅልሎ ውበት ያላበሳቸው፣

በጃማይካና ደቡብ አፍሪካውያን የነጻነት ታጋዮች እጅ በፍቅር ተይዞ አየሩን እየቀዘፈ የሚውለበለበው አረንጓዴ
ቢጫ ቀይ ቀለማትን የያዘው የኢትዮጵያ ባንዲራ ነው፡፡

ባልጠበኩት ክስተት እጅግ ተገረምኩ ሲቃ ተናነቀኝ አይኖቼ የእንባ ጤዛ ቋጠሩ፡፡
የጊዜ መንኮራኩሩን ወደተነሳሁበት 2016 ዓ.ም መለስኩት ። አቶ አይነኩሉ የሀገሬ ባንዲራ በአፍሪካ ሀገራት
ያላትን ክብር እያወጉኝ የዘንድሮ የሰንደቅ አላማ በዓል ወደ ሚከበርበት አዳራሽ ገባን፡፡

በአዳራሹ በአሉን ለማክበር የደቡብ ክልል ምክር ቤት ብሔረሰቦች ምክር ቤት ፣የርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤትና
የክልሉ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሰራተኞች ታድመዋል፡፡

ሁሉም ታዳሚ የኢትዮጵያንና የክልሉን ባንዲራ በእጁ ይዟል፡፡

የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ የመክፈቻ ንግግር አደረጉና ቦታቸውን ያዙ ። መድረኩ ላይ አቶ አይነኩሉ
ወጥተው ለፓናል ውይይት የሚሆን ጽሁፍ ማቅረብ ጀመሩ ። የለንደኑን የስብሰባ አዳራሽ ድባብ ሲያወጉ ሁሉም
በመገረም ያዳምጣል ፡፡

በአንድ ወቅት ከጎግል ድረገጽ ላይ አውርጄ ያነበብኩት why do African flags all have similar
color? በሚል ርዕስ የተጻፈ አንድ ጽሁፍ ትውስ አለኝ፡፡

ጸሀፊው በአንድ አጋጣሚ በአፍሪካ ውስጥ ወደተለያዩ ሀገራት በሚጓዝበት ወቅት በመኪናው ውሰጥ የነበሩ ዘጠኝ
የሚጓዝባቸው ሀገራት ባንዲራዎች ቀለም መመሳሰልን ማሰተዋሉ ለምንድ ነው የአፍሪካ ሀገራት ባንዲራዎች ቀለም
የተመሳሰለው? የሚል ጥያቄ ተፈጠረበት፡፡

ምክንያቱ  ደግሞ የአውሮፓ ሀገራት አፍሪካን ተቀራምተው በነበረበት የቅኝ ግዛት ዘመን በጀግኖች ልጆቿ ተጋድሎ
ሳትደፈር በነጻነት የኖረች አንድ ብቸኛ ሀገር ነበረች፡

ይቺ ሀገር ለሉዋዕላዊነቷና ለነጻነቷ ምልክት የሆነ በአረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀለማት ህብር የደመቀ አላማ ባለቤት ናት-
ኢትዮጵያ ፡፡
በጣሊያን ተወራ ከቆየችባቸው አምስት ዓመታት በስተቀር እንደሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ገዥዎች ያልተደፈረች
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አባል ከነበሩ አራት ሀገራት መካከል አንዷና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መስራች
መሆኗ በቅኝ ለተያዙት ሀገራት ምልክት ተደርጋ ትወሰድ ነበር፡፡

ሁለተኛው የአለም ጦርነትን ተከትሎ በቅኝ ግዛት ስር ሲማቅቁ የቆዩ የአፍሪካ ሀገራት ነጻነታቸውን ሲቀዳጁ በርካቶቹ
ለባንዲራቸው መነሻ የሆነውን አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀለም ከኢትዮጵያ ባንዲራ መውረሳቸውን በጽሁፉ ተካቷል፡፡
ይህን የኢትዮጵያ ባንዲራ ቀለም ወስዳ የራሳን ልዩ ምልክት በማድረግ ጥቅም ላይ ያዋለች የመጀመሪያዋ ሀገርም
ጋና ናት፡፡
ያኔ የጋና መሪ የነበሩት ክዋሚ ንክሩማህ የኢትዮጵያን ባንዲራ ቀለም አቀማመጥ በመገልበጥ በመሀሉ ላይ ጥቁር
ኮከብ በማድረግ የሀገራቸው ባንዲራ መሆኑን አወጁ፡፡

ጋናን በመከተል ቦርኪናፋሶ ፣ካሜሮን ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ፣ ሁለቱ ኮንጎዎች ፣ ማሊ ፣ ቤኒን ፣ጊኒና ኢኳቶሪያል
ጊኒ፣ ሞዛምቢክ ፣ሶአቶሜና ፕሪንሲፔ ፣ ሴኔጋል ፣ ደቡብ አፍሪካ ፣ ቶጎና ዚምባቡዌ በቅርቡ ዕውቅና ያገኘችው
ደቡብ ሱዳን በባንዲራቸው ውስጥ የኢትዮጵያ ቀለማትን አካተዋል፡፡

እንዲሁም ከካሪቢያን ሀገራት ግሪናዳና ሴንት ኪትስና ኔቪስ የኢትዮጵያን ቀለም ጥቅም ላይ ያዋሉ ሀገራት ናቸው፡፡
እነዚህ የአፍሪካና የካሪቢያን ሀገራት የኢትዮጵያን ቀለማት በመውሰድ የራሳቸውን ምልክት በማካተት ባንዲራቸውን
አዘጋጅተዋል፡፡

ይህ ብቻ አይደለም ለአህጉሩ ትልቅ የነጻነት ምልክት ተደርጋ የምትወሰደው ኢትዮጵያ የበርካታ አህጉራዊና አለም
አቀፋዊ ድርጅቶች ዋና ጽህፈት ቤት መገኛ እንድትሆን አስችሏታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያን ቀለማትን አረንጋዴ ቢጫና ቀይ እንዲሁም የፓን አፍሪካ ቀለማት ቀይ አረንጓዴና
ጥቁር ቀለማትን በማዋሃድና የራሳቸውን ልዩ ምልክት በማድረግ ለባንዲራቸው ቀለም የሰጡ የፓን አፍሪካኒዝም
አቀንቃኝ የሆኑ የአፍሪካና የካሪቢያን ሀገራት አሉ፡፡

ኬንያ ሊቢያ ማላዊና ዛምቢያ ከአፍሪካ ከካሪቢያን ሀገራት ውስጥ ደግሞ ጃማይካ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ከሀገራቱ ባለፈ የራስ ተፈሪያን እንቅስቃሴ አራማጆችና ሌሎች የፓን አፍሪካን እንቅስቃሴ ተቋማት አርማቸውን
በኢትዮጵያ ቀለማት መነሻ አድርገዋል፡፡

የፓናል ውይይቱ ተጠናቆ ባንዲራ የመስቀል ስነስርዓት ለማከናወን ታዳሚው ከአዳራሽ ወጣ፡፡
ሁሉም አርማዋን ለመስቀል በሰነደቁ ዙሪያ ቆመ፡፡

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት የችሎት ካባቸውን ደርበው ቃለ መሀላ ለማስገባት ተዘጋጅተዋል፡፡
የኢትዮጵያና የክልሉ ሰንደቅ አላማዎች በክልሉ ልዩ ኋይል በክብር ታጅበው ወደ መስቀያው  ቀረቡ፡፡
የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤና የርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሁለቱን ሰንደቅ አላማዎች ለመስቀል
ቦታቸውን ያዙ፡፡
በመሀል አነስተኛ በራሪ ወረቀት ለሁላችንም እየዞረ ታደለ፡፡

በራሪ ወረቀቱ የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙርን የያዘ ነው፡፡ የሚገርመው ይህ መዝሙር ጥቅም ላይ ከዋላ ከሁለት
አስርት አመታት በላይ ሆኖታል፡፡ ነገር ግን ሁላችንም አናውቀውም፡፡

ፊሽካ ተነፋ ። ሰንደቁ መሰቀል ጀመረ ። ሁሉም በበራሪ ወረቀት ተጽፎ የተሰጠውን መዝሙር እያነበበ መዘመር
ጀመረ ። ከሁሉም ጎልቶ የሚሰማው ግን በቴፕ የተከፈተው መዝሙር ነበር፡፡
ሁሉም ሲዘምር ለመታዘብ ዙሪያውን መቃኘት ጀመርኩ ።ከተወሰኑ በጣት ከሚቆጠሩ ሰዎች በስተቀር በቃሉ
መዝሙሩን የሚዘምር የለም ፡፡
እነጆሞ ኬንያታ፣  ክዋሚ ንክሩማህ ሌሎች የአፍሪካና የካሪቢያን ሀገራት መሪዎች ለሀገሪ ሰንደቅ አላማ የሰጡትን
ያህል ክብር በኔ ውስጥ አለ እንዴ? ስል ራሴን ጠየቅሁ፡፡

ጀግኖች አትሌቶቻችን በአለም አደባባይ ከፍከፍ አድርገዋታል፡፡ ባንዲራዋ ከፍ ሲል እንባቸው የአይናቸውን ግድብ
ጥሶ ጉንጫቸውን እያራሰ ሲወርድ አስተውያለሁ፡፡

እኔ ግን ክብር እንዳልሰጠኋት የተረዳሁበት ቀን ዛሬ መሆኑን ተረድቻለሁ ። ክብር ብሰጣትማ ኖሮ መዝሙሯን
በቃሌ መዘመር በቻልኩ ነበር፡፡

ራስ ተፈሪያን በአለባበስ አጊጠውና ተውበው የሚወጡት በሀገሬ ባንዲራ ነው፡፡

በርካታ የአፍሪካ ሀገራት አክብረው እንደ ምሰሶ የሚያዩአትን ሰንደቅ ያላከበርኳት እኔ ማነኝ?
በየአደባባዩ በእሳት እያቃጠልኩ ክብሯን የገፈፍኳት እኔ ማነኝ?

አዎ በዛ አዳራሽ የታደሙ የሌላ ሀገር ሰዎች የሰጧትን ፍቅርና ክብር እኔ ባለቤት ሆኜ የነፈግኋት ለምንድን ነው?
እኔ ማን ነኝ?
የነፈግኋትን ክብር መልሼ መዝሙራን በቃሌ እየዘመርኩ ከፍ ከፍ ላደርጋት ለራሴ ቃል ገባሁ፡፡
አቶ አይነኩሉ የጊዜ መንኮራኩር ሆነው ወደ ኋላ መልሰው ራሴን አሳዩኝ  ። እንደነ ክዋሚ ንክሩማህ እንደ ጆሞ
ኬንያታ ለሀገሬ ሰንደቅ አላማ  ክብር ልሰጥ ቃል ገባሁ፡፡
     
                                                                                                                                                           ቸር
እንሰንብት!