1
    HEBREZEMA.INFO
    INDEPENDENT NEWS & MEDIA
    DESIGNED BY ZEWDU TEKLU
    © COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED 2007.
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈፃሚ ኮማንድ ፖስት የዲፕሎማቶች እንቅስቃሴ ክልከላን ሙሉ በሙሉ አነሳ
November 08,2016
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈጻሚ ኮማንድ ፖስት ከአሁን ቀደም
በወጣው መመሪያ ላይ ተጥሎ ከነበሩ ክልከላዎች መካከል ያለፍቃድ የሚደረግ የዲፕሎማቶች እንቅስቃሴ ክልከላን
ሙሉ በሙሉ ማንሳቱን አስታወቀ።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈጻሚ ኮማንድ ፖስት መመሪያ ቁጥር ሁለትን በዛሬው እለት ይፋ ያደረገ ሲሆን፥ መመሪያ
ቁጥር ሁለት በእርምጃዎች ላይም የተወሰኑ ማሻሻያዎቸን አድርጓል።

በዛሬው እለት ይፋ የተደረገው መመሪያ በአጠቃላይ አራት ክፍሎች እና ዘጠኝ ድንጋጌዎችን በውስጡ ያካተተ ነው።

ከእነዚህ ድንጋጌዎች ወስጥ ሙሉ በሙሉ እና በከፊል የተነሱ ክልከላዎችን የተመለከቱት ሁለት ሲሆኑ፥
የመጀመሪያው ያልተፈቀዱ አልባሳትን መልበስ ነው።

ከአሁን ቀደም በወጣው እና ባለፉት ሶስት ሳምንታት በተተገበረው መመሪያ ላይ ማንኛውም ሰው የፀጥታ ሀይል
አስከባሪ የደምብ ልብስን ይዞ ቢገኝ፣ ቢለብስ፣ ለሶስተኛ ወገን አሳልፎ ቢሰጥ ወይም ደግሞ ቢሸጥ በህግ እንደሚቀጣ
እና መሰል ተግባራትን ማከናወን የተከለከለ እንደሆነ ይደነግግ ነበር።

በዛሬው እለት ይፋ የተደረገው መመሪያ ሁለት ግን የህግ አስከባሪዎችን የደምብ ልብስ ይዞ መገኘት ወይም በቤት
ውስጥ ማስቀመጥን አስመልክቶ የተደረገው ክልክላ በመመሪያ ቁጥር ሁለት ተነስቷል ብሏል።

ተከልክለው ከነበሩት መካከል የተነሳው በቤት ውስጥ ማስቀመጥ እና ይዞ መገኘት ብቻ ነው።

የኮማንዱ ፖስቱ ሴክረተሪያት እና የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ፥ “ይህ ሊሆን የቻለው በተለያዩ የሀገሪቱ
ክፍሎች ከሚገኙ የህብረተሰብ አካላት ጋር በተደረገ ውይይት በተለያየ ምክንያት እጃቸው የገባ የህግ አስከባሪዎች
የደንብ ልብስ አለ፤ የደንብ ልብሱን በየቤታቸው አስቀምጠው የሚገኙ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመውጣቱ በፊት
ለብሰው የተለያዩ የማህበራዊ ህይወትን የሚከውኑበት እና እንደ መደበኛ ልብስ የሚጠቀሙበት መሆኑን በማንሳታቸው
ነው” ብለዋል።

“ይዘን መገኘት እና በቤት ወስጥ ማስቀመጥን እንዴት እንከለከላለን? የሚል ጥያቄ ስላቀረቡ ይዞ መገኘት እና
በቤት ውስጥ ማስቀመጥ የሚለው ክልከላ ተነስቷል፤ ነገር ግን መልበስ እና ለሶስተኛ መገን አሳልፎ መስጠት መይም
መሸጥ አሁንም የተከለከለ ነው” ብለዋል።

ሁለተኛው ክልከላ የተነሳበት ያለ ፈቃድ ስለሚደረግ የዲፕሎማቶች እንቅስቃሴ ነው።

ከአሁን በፊት በወጣው መመሪያ ላይ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ለራሱ ደህንነት ሲባል ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር
ዙሪያ ውጭ ሲንቀሳቀሱ ለኮማንድ ፖስቱ ማሳወቅ አለባቸው የሚል ሲሆን፥ አሁን ይህ ክልከላ ሙሉ በሙሉ ተነስቷል።

ምክንያቱ ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲታወጅ በሀገሪቱ የነበረው የሰላም እና የደህንነት ስጋት እና አሁን ያለው
የተለያየ መሆኑን የገለፁት አቶ ሲራጅ፥ ሀገሪቱ በአንፃራዊነት ወደ ሰላም እና መረጋጋት በመመለሷ የዲፕሎማቲክ
ማህበረሰቡ በፈለገው የሀገሪቱ ክፍል ቢንቀሳቀስ የሰላም እና የደህንነት ስጋት ስለሌለ ክልከላውን ማንሳት አስፈላጊ
ሆኗል ነው ያሉት።

ከዚህ በተጨማሪም በመመሪያ ቁጥር በተለያዩ እርምጃዎች ላይ ማሻሻያ መደረጉ የተገለፀ ሲሆን፥ ከነዚህ ውስጥ
አንዱ የፀጥታ አስከባሪው ሀይል ራሱን ለመከላከል ስለሚወስደው እርምጃ የሚመለከተው ነው።

ከዚህ ቀደም በወጣው መመሪያ ላይ የድርጅት ጥበቃ እና ፀጥታ የማስከበር ስራ ላይ የተሰማሩ ሀይሎች
ህይወታቸውን እና ንብረታቸውን አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት በጦር መሳሪያና በስለት ሊፈፀምባቸው ከተቃጣ
ራሳቸውን ለመከላከል እርምጃ ይወስዳሉ ይላል።

ዛሬ ይፋ በተደረገው እና በተሻሻለው መመሪያ ቁጥር ሁለት ላይ ደግሞ የህግ አስከባሪዎች እና የድርጅት ጥበቃ ላይ
የተሰማሩ ሰዎች ራሳቸውንና የራሳቸውን ንብረት ብቻ ሳይሆን፥ የሚጠብቁትን ህብረተሰብና ድርጅት አደጋ ላይ ሊጥል
የሚችል ድርጊት በጦር መሳሪያ፣ በስለት፣ በሀይል ወይም በሌላ ማንኛውም ዘዴ አማካኝነት በህይወት፣ በአካል እና
በንብረት ላይ ጉዳይ የሚያደርስ ከሆነ ያን ጉዳት ለመከላከል የሚያስችል እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ በሚል ተሻሽሏል።

ብርበራ ወይም ፍተሻን በተመለከተ ወጥቶ በነበረው መመሪያ ላይም ማሻሻያ መደረጉም ተመልክቷል።

ከአሁን በፊት በነበረው መመሪያ ላይ ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ የህግ አስከባሪ አካላት ብርበራ ማከናወን ይችላሉ
የሚል ነው።

በመመሪያ ቁጥር ሁለት ላይ በብርበራ ዙሪያ ዝርዝር ሁኔታዎች ተካቶ ማሻሻያ የተደረገ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ
ማንኛውም የህግ አስከባሪ አካል ብርበራ በሚያደርግበት ጊዜ መታወቂያ የማሳየት እና ብርበራውን የሚያደርግበትን
ምክንያት የማሳወቅ ግዴታ አለበት የሚለው ተካቷል።

እንዲሁም ብርበራው የሚካሄድባቸው ሰዎች የብርበራ ሂደቱን እንዲከታተሉ መፍቀድ እና በርባሪው አካል ብርበራውን
በሚደረግበት ወቅት የአካባቢው ፖሊሶችና የማህበረሰቡ ተወካዮች በታዛቢነት እንዲከታተሉ የማድረግ ግዴታ አለበት
የሚለውም በማሻሻያው ተካቷል።

አዲስ በወጣው መመሪያ ቁጥር ሁለት ላይ ሚስጥር መጠበቅ የሚል አዲስ ድንጋጌም መካተቱምተገልጿል።

በዚህም ማንኛውም በብርበራ እና በፍተሻ ላይ የተሳተፈ የህግ አስከባሪ አካል ብርበራ እና ፍተሻውን ከማካሄዱ
በፊትም ይሁን በኋላ ያገኛቸውን መረጃዎች ለሚመለከተው አካል ከማሳወቅ ውጭ መረጃዎቹን በሚስጥር የመያዝ
ግዴታ አለበት ተብሏል።


በዳዊት መስፍን
admin@hebrezema.info
1