1
    HEBREZEMA.INFO
    INDEPENDENT NEWS & MEDIA
    DESIGNED BY ZEWDU TEKLU
    © COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED 2007.
በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ካቢኒ አባልነት የተሾሙት እነማን ናቸው?
October 23, 2016
በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ካቢኒ አባልነት የተሾሙት እነማን ናቸው?

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጨፌ ኦሮሚያ ባካሄደው አምስተኛ የሥራ ዘመን ሁለተኛ ዓመት ሁለተኛ አስቸኳይ
ስብሰባ አቶ ለማ መገርሳን የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርእሰ መስተዳድር አድርጎ ሾሟል።

ይህንንም ተከትሎ አዲሱ ርእሰ መስተዳደር የክልሉን መንግስት ካቢኒ አባላት ለጨፌው አቅርበው አስፀድቀዋል።

በአቶ ለማ መገርሳ ቀርበው ሹመታቸው በጨፌው ከፀደቀ በኋላ ቃለ መሃላ ከፈፀሙት 21 ተሿሚዎች መካከል 16ቱ ከዚህ ቀደም በካቢኒ
ውስጥ ያልነበሩ አዳዲስ ተሿሚዎች ናቸው።

ከእነዚህ ውስጥም ስምንቱ የኦህዴድ አባል ያልሆኑ እና በጥናት እና ምርምር ላይ ተሰማርተው የነበሩ ምሁራን ናቸው።

የካቢኒ አባላቱ ዝርዝር የህይወት፣ የትምህርት እና ስራ ዳራ እንደሚከተለው ቀርቧል።

አቶ ኡመር ሁሴን ኡባ

የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳድር

የትውልድ ስፍራ፦ አርሲ ዞን

የትምህርት ዝግጅት፦ የመጀመሪያ ዲግሪ በኢኮኖሚክስ፣ ሁለተኛ ዲግሪ በኢንተርናሽናል ቢዝነስ።

የስራ ልምድ፦ በአርሲ ዞን የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት መምሪያ ሃላፊ፣ ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ሃላፊ፣ የከተማ ልማት
መምሪያ ሃላፊ በመሆን እና በተለያዩ ስፍራዎች በሃላፊነት ሲሰሩ ቆይተዋል።

በመቀጠልም የአርሲ ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣ የኦሮሚያ ክልል የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ እና ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል
ሃላፊ በመሆን አገልግለዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል የግብርና ቢሮ ሃላፊ በመሆንም ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

በአሁኑ ጊዜም በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት እና ቤቶች ቢሮ ሃላፊ በመሆን በመስራት ላይ ነበሩ።
እንዲሁም አቶ ኡመር ሁሴን የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ናቸው።

አቶ አብይ አህመድ አሊ

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት እና ቤቶች ቢሮ ሃላፊ

የትውልድ ስፍራ፦ ጅማ ዞን

የትምህርት ዝግጅት፦ የመጀመሪያ ዲግሪ በኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ፣ ሁለተኛ ዲግሪ በትራንፎርሜሽናል ሊደርሺፕ እና ቼንጅ፣ ማስተርስ
ኢን ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን እንዲሁም በክሪፕቶ ግራፊ ያላቸው ሲሆን፥ በአሁኑ ጊዜም በ“ፒስ ኤንድ ሴክዩሪቲ” የዶክትሬት
ትምህርታቸውን በመከታታል ላይ ይገኛሉ።

የስራ ልምድ፦ በመከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ እስከ ሌፍተናንት ኮሎኔል ድረስ በተለያዩ ስፍራዎች ሲያገለግሉ ቆይተዋል፣ የፌዴራል ሳንስስ
እና ቴክኖሎጂ የልህቀት ማእከል ዋና ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል፣ በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ውስጥም በምክትል
ዳይሬክተርነት አገልግለዋል፣ በአሁኑ ጊዜም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በመሆን በማገልገል ላይ ነበሩ።

አቶ አብይ አህመድ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ናቸው።

አቶ ስለሺ ጌታሁን

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የእርሻ እና የተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ሃላፊ

የትውልድ ስፍራ፦ ምስራቅ ሀረርጌ ዞን

የትምህርት ዝግጅት፦ በአግሪከልቸራል ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው።

የስራ ልምድ፦ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሌክቸረር በመሆን ለረጅም ጊዜ አገልግለዋል፣ የኦሮሚያ መስኖ ልማት ባለስልጣን ውስጥ ከፍተኛ የመስኖ
ባለሙያ በመሆን አገልግለዋል፣ በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሃብት ዋና ዳይሬክተር እና ሚኒስትር ዴኤታ በመሆንም አገልግለዋል፣
የኢፌዴሪ የእንስሳት እና አሳ ሀብት ሚኒስትር በመሆንም ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

እንዲሁም አቶ ስለሺ ጌታሁን የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ናቸው።

አቶ ቶሎሳ ገደፋ

የክልሉ የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ሀላፊ

የትውልድ ስፍራ፦ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ

የትምህርት ዝግጅት፦ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪ በኢኮኖሚክስ

የስራ ልምድ፦ የዞን የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት መምሪያ ሃላፊ፣ የኦሮሚያ ገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ እና ሃላፊ
በመሆን አገልግለዋል፣ የስኳር ኮርፖሬሽን ምክትል ስራ አስኪያጅ በመሆን ሲያገለግሎ የቆዩ ሲሆን፥ የኢፌዴሪ የመንግስት ልማት
ድርጅቶች ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ በመሆን ሲያገለግሉ ነበር።

አቶ ቶሎሳ ገደፋ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ናቸው።

አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ

የክልሉ የፍትህ ቢሮ ሃላፊ

የትውልድ ስፍራ፦ ደቡብ ምእራብ ሸዋ ዞን

የትምህርት ዝግጅት፦ የመጀመሪያ ዲግሪ በህግ፣ ሁለተኛ ዲግሪ በአመራር።

የስራ ልምድ፦ የምስራቅ ሀረርጌ ዞን የፍትህ እና አስተዳደር መምሪያ ሀላፊ፣ የደቡብ ምእራብ ሸዋ ዞን የህዝብ ግንኙነት ቢሮ ሃላፊ፣
የኦሮሚያ ፍትህ ቢሮ ምክትል ሃላፊ፣ የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን፥ በአሁኑ ጊዜም የኦሮሚያ
ኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊ በመሆን በማገልገል ላይ ነበሩ።

እንዲሁም አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ናቸው።

ዶክተር ደረጀ ጉደታ

የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ

የትውልድ ስፍራ፦ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ

የትምህርት ዝግጅት፦ የመጀመሪያ ዲግሪ በሜዲካል ዶክትሬት፣ ሁለተኛ ዲግሪ ኢንተርናሽናል ሄልዝ

የስራ ልምድ፦ የሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር፣ በክልል የጤና ጥበቃ ቢሮ የበጀት እና እቅድ ክትትል ስራ አስኪያጅ፣ የጤና ቢሮ ሃላፊ
አማካሪ በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን፥ የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

ዶክተር ሀሰን የሱፍ

የክልሉ የደን እና አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ቢሮ ሃላፊ

የትውልድ ስፍራ፦ ምስራቅ ወለጋ ዞን

የትምህርት ዝግጅት፦ የመጀመሪያ ዲግሪ በእፅዋት ሳይንስ፣ ሁለተኛ ዲግሪ በቦታኒካል ሳይንስና በዴቨሎፕመንታል ስተዲስ፣ እንዲሁም
በናቹራል ሪሶርስ ማናጅመንት የዶክትሬት ዲግሪ አላቸው።

የስራ ልምድ፦ በባኮ የእርሻ ምርምር ማዕከል ውስጥ በተመራማሪነት ሰርተዋል፣ በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት
ዘርፍ በሃላፊነት አገልግለዋል፤ በአሁኑ ጊዜም የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን በማገልገል ላይ ነበሩ።

ዶክተር ተሾመ አዱኛ

የክልሉ የእቅድ እና ኢኮኖሚ ልማት ኮሚሽን ቢሮ ሃላፊ

የትውልድ ስፍራ፦ አዲስ አበባ

የትምህርት ዝግጀት፦ የመጀመሪያ ዲግሪ በኢኮኖሚክስ እንዲሁም ሁለተኛ እና ዶክትሬት ዲግሪ በዴቬሎፕመንታል ኢኮኖሚክስ፤ በአጠቃላይ
የትምህርት ዝግጅታቸው በረዳት ፕሮፌሰር ደረጃ ላይ የደረሰ ነው።

የስራ ልምድ፦ በኦሮሚያ ጤና ቢሮ የፕሮጀክት ባለሙያ በመሆን በሃላፊነት አገልግለዋል፣ በአሁኑ ጊዜም በዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ
አገልግሉት ዳይሬክተር እና ሌክቸረር በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

አቶ ሀብታሙ ሀይለሚካኤል

የክልሉ የወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ

የትውልድ ስፍራ፦ ኢሉ አባቦራ ዞን

የትምህርት ዝግጅት፦ በኦርጋናይዜሽናል ማኔጅመንት ኤንድ ሊደርሺፕ እና በአግሪካልቸራል ኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪ።

የስራ ልምድ፦ የወረዳ የግብርና ፅህፈት ቤት ሃላፊ፣ የያዮ ወረዳ አስተዳደሪ፣ የደቡብ ምእራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ፣ የሻሸመኔ ከተማ
ከንቲባ በመሆን ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ ሲሆን፥ በአሁኑ ጊዜ የአዳማ ከተማ ከንቲባ በመሆን ሲያገለግሉ ነበር።
እንዲሁም አቶ ሀብታሙ ሀይለሚካኤል የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል በመሆንም ያገለግላሉ።

ኢንጂነር ብርሃኑ በቀለ

የክልሉ የኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊ

የትውልድ ስፍራ፦ ምእራብ አርሲ ዞን

የትምህርት ዝግጅት፦ በአግሪካልቸራል ኢንጂነሪንግና በሲቪል ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም ሁለተኛ ዲግሪ በህይድሮሊክስ
ኢንጂነሪንግ።

የስራ ልምድ፦ በኦሮሚያ መስኖ ልማት ባለስልጣን በአራት ዞኖች አመራር በመሆን አገልግለዋል፣ በመቀጠልም በኦሮሚያ መስኖ ልማት
ባለስልጣን ከፍተኛ መሃንዲስ በመሆን ሰርተዋል፣ የኦሮሚያ ውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ምክትል ስራ አስኪያጅ፣ የኦሮሚያ
መንገዶች ባለስልጣን ሃላፊ በመሆን እንዲሁም የኦሮሚያ መንገዶች ግንባታ ኢንተርፕራይዝ ሃላፊ በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን፥ በአሁኑ
ጊዜም የልማት ስራዎች አስተባባሪ ዳይሬክተር በመሆን ሲያገለግሉ ነበር።

ረዳት ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረሚካኤል

የክልሉ የአስተዳደር እና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ

የትውልድ ስፍራ፦ ምእራብ ሸዋ ዞን

የትምህርት ዝግጅት፦ በፖሊስ ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም በአመራር ሳይንስ እና በፐብሊክ አድሚኒስትሬሽን ሁለተኛ ዲግሪ
አላቸው።

የስራ ልምድ፦ በኦሮሚያ ክልል ከወረዳ አንስቶ እስከ ክልል የፖሊስ አመራር፣ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር እንዲሁም በፌደራል
ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል።

በአሁኑ ጊዜም የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ዋና ዳይሬክተር በመሆን ሲያገለግሉ ነበር።

ወይዘሮ ሎሚ በዶ

የክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ

የትውልድ ስፍራ፦ ምስራቅ ሸዋ

የትምህርት ዝግጅት፦ በቋንቋ ዲፕሎማ እንዲሁም በህግ የመጀመሪያ ዲግሪ አላቸው።

የስራ ልምድ፦ የወረዳ የማህበራዊ አገልግሎት ቢሮ ሃላፊ፣ የወረዳ አፈ ጉባዔ በመሆን እንዲሁም የዱድጋ ወረዳ አስተዳዳሪ በመሆን፣
በኦሮሚያ ክልል የአደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር በመሆን ያገለገሉ ሲሆን፥ በአሁኑ ጊዜም የክልሉ ንግድ እና
ገበያ ልማት ቢሮ ሃላፊ በመሆን ሲያገለግሉ ነበር።
እንዲሁም ወይዘሮ ሎሚ በዶ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል በመሆን በማገልገል ላይ ናቸው።

አቶ አሰፋ ኩምሳ

የክልሉ የውሃ፣ ማዕድን እና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊ

የትውልድ ስፍራ፦ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ

የትምህርት ዝግጅት፦ የመጀመሪያ ዲግሪ በጂኦሎጂ እንዲሁም ሁለተኛ ዲግሪ በጂኦ ኢንፎርሜሽን ሳይንስ።

የስራ ልምድ፦ የልማት ስራዎች ፕሮጀክት አመራር በመሆን፣ የኦሮሚያ ውሃ ስራዎች ዲዛይን እና ቁጥጥር ድርጅት ሃላፊ በመሆን
ያለገለገሉ ሲሆን፥ በአሁኑ ጊዜም በኔዘርላንድስ በሚገኝ ኩባንያ ውስጥ ከፍተኛ ዳይሬክተር በመሆን ሲሰሩ ነበር።

ወይዘሮ አዚዛ አህመድ

የክልሉ የሴቶች እና የህፃናት ቢሮ ሃላፊ

የትውልድ ስፍራ፦ ምእራብ ሀረርጌ ዞን

የትምህርት ዝግጅት፦ የመጀመሪያ ዲግሪ በአፕላይድ ባዮሎጂ እንዲሁም ሁለተኛ ዲግሪ በማስተርስ ኦፍ ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን አላቸው።

የስራ ልምድ፦ የጭሮ ወረዳ ምትክል አስተዳዳሪ፣ የዞን የትምህር፣ የትራንስፖርት እና የመንገዶች ባለስልጣን መምሪያዎች ሃላፊ እንዲሁም
የድሬደዋ ከተማ የሴቶች፣ ህፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ በመሆን ያለገለገሉ ሲሆን፥ በአሁኑ ጊዜም የኦሮሚያ ወጣቶች እና
ስፖርት ቢሮ ሃላፊ በመሆን በማገልገል ላይ ነበሩ።
እንዲሁም ወይዘሮ አዚዛ አህመድ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል በመሆን በማገልገል ላይ ናቸው።

አቶ ወንድማገኝ ነገራ

የክልሉ ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ሃላፊ

የትውልድ ስፍራ፦ ቄለም ወለጋ ዞን

የትምህርት ዝግጅት፦ በአካውቲንግ የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም ሁለተኛ ዲግሪ በቢዝነስ ሊደርሺፕ አላቸው።

የስራ ልምድ፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጅማ ቅርንጫፍ ማናጀር፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በምክትል ፕሬዚዳንትነት እንዲሁም የኦሮሚያ
ህብረት ስራ ባንክ ፕሬዚዳንት በመሆን አገልግለዋል።

አቶ ካሳዬ አብዲሳ

የክልሉ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት እና ስልጠና ቢሮ ሀላፊ

የትውልድ ስፍራ፦ ምእራብ ሸዋ ዞን

የትምህርት ዝግጅት፦ የመጀመሪያ ዲግሪ በማኔጅመንት እንዲሁም ሁለተኛ ዲግሪ በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ማኔጅመነት አላቸው።

የስራ ልምድ፦ በመምህርነት፣ በዞን ትምህርት መምሪያ ሱፐርቫይዘር፣ የአዳማ እና ጭሮ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ዲን፣ በአሁኑ
ጊዜም የኦሮሚያ በብቃት ማረጋገጫ ኤጀንሲ ሃላፊ በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

አቶ ብርሃኑ ፈይሳ

የርዕሰ መስተዳድሩ ጽህፈት ቤት ቢሮ ሃላፊ

የትውልድ ስፍራ፦ ሰሜን ሸዋ ዞን

የትምህርት ዝግጅት፦ በኢዱኬሽናል ማናጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም በኤዱኬሽናል ፕላኒንግ ኤንደ ሊደርሺፕ ትምህርት
ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው።

የስራ ልምድ፦ በትምህር ቤቶች ውስጥ በአመራርነት በተለያየ ደረጃ ሰርተዋል፣ በፀጥታ እና አስተዳዳር ቢሮ ውስጥ የእቅድ ባለሙያ
በመሆን አገልግለዋል፣ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ውስጥ የመድሃኒት አቅርቦት መምሪያ ሃላፊ እና የቢሮ ሃላፊ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን፥
በአሁኑ ጊዜም በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የፌዴራል ኤች.አይ.ቪ መከላከል ቢሮ ሃላፊ በመሆን በማገልገል ላይ ነው ነበሩ።

አቶ ኤልማ ቃምጴ

የክልሉ ዋና ኦዲተር

የትውልድ ስፍራ፦ ቦረና ዞን

የትምህርት ዝግጅት፦ የመጀመሪያ ዲግሪ አላቸው።

የስራ ልምድ፦ የዞን ትምህርት ቢሮ ሃላፊ፣ የዞን ገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሃላፊ፣ የኦሮሚያ ክልል ገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት
ቢሮ ምክትል ሃላፊ በመሆን ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ ሲሆን፥ በአሁኑ ጊዜም የክልሉ የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ሀላፊ በመሆን
ሲያገለግሉ ነበር።

ወይዘሮ ሂሩት ቢራሳ

ክልሉ የስነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር

የትውልድ ስፍራ፦ ምእራብ ወለጋ ዞን

የትምህርት ዝግጅት፦ በህግ የመጀመሪያ ዲግሪ አላቸው።

የስራ ልምድ፦ በአዲስ አበባ ከተማ እና በክልል የድርጅት ቢሮ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ሲያገለግሉ ቆይተዋል፤ እንዲሁም በህዝብ ተወካዮች
ምክር ቤት የሴቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሜቴን ሲመሩ ቆይተዋል፤ በመቀጠልም የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን የፍትህ መምሪያ ሃላፊ በመሆን ያገለገሉ
ሲሆን፥ በአሁኑ ጊዜም የሴቶች እና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ በመሆን ሲሰሩ ነበር።
እንዲሁም ወይዘሮ ሂሩት ቢራሳ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል በመሆን በማገልገል ላይ ናቸው።

አቶ ጌቱ ወዬሳ

የኦሮሚያ ራዲዮ እና ቴሌቭዥን ድርጅት ዳይሬክተር

የትውልድ ስፍራ፦ አርሲ ዞን

የትምህርት ዝግጅት፦ የመጀመሪያ ዲግሪ በማኔጅመንት እንዲሁም ሁለተኛ ዲግሪ በሊደርሺብ አላቸው።

የስራ ልምድ፦ የወረዳ አመራር በመሆን፤ በአርሲ፣ በባሌ እና በምእራብ እርሲ ዞኖች የድርጅት አመራር በመሆን፣ የክልሉ ከተማ ልማት
እና የኢንደስትሪ ቢሮ አማካሪ በመሆን፣ የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን የፖለቲካ አደረጃጀት አመራር በመሆን ሲያገለግሉ የነበረ ሲሆን፥ በአሁኑ
ጊዜ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ ሆነው ሲያገለግሉም ነበር።በሙለታ መንገሻ
admin@hebrezema.info
1