1
    HEBREZEMA.INFO
    INDEPENDENT NEWS & MEDIA
    DESIGNED BY ZEWDU TEKLU
    © COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED 2007.
አዲስ የሚዋቀረው ካቢኔ ስር ነቀል ለውጥን የሚያመጣ መሆን እንዳለበት ምሁራኑ ተናገሩ
October 31,2016
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 21 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲሱ የፌደራል መንግስት ካቢኔ ነገ ለህዝብ ተወካዮች ምክር
ቤት እንደሚቀርብ ይጠበቃል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው ምሁራን መንግስት የተሃድሶ አንድ አካል ነው ያለው፥ አስፈፃሚውን አካል
የማዋቀር ውሳኔ ጥገናዊ ሳይሆን ስር ነቀል ለውጥን የሚያመጣ መሆን አለበት ብለዋል።

ምሁራኑ እንደሚሉት መንግስት ስር ነቀል ለውጥ በማምጣትና አጠቃላይ ችግሮቹን ነቅሶ በማውጣት አዲስ ነገር
መፍጠር መቻል አለበት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ፥ ከወራት በፊት የፌደራል መንግስቱን ካቢኔ እንደ አዲስ ማዋቀር የተሃድሶ
እንቅስቃሴው አንድ አካል ይሆናል ብለው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገቡት ቃል መሰረት አዲሱ ካቢኔያቸውን ነገ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚያቀርቡ
ይጠበቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ካሁን ቀደም ባደረጉት ንግግር የመንግስት ዋናው ችግር ስልጣንን የራስ ጥቅም
ማስፈፀሚያ ያደረጉ ከስራ አስፈፃሚው እስከ ተቋማት አመራር ያሉ ግለሰቦችን አቅፎ መያዙ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት እና ስትራቴጂ ጥናት ኢኒስቲቲዩት የከባቢያዊ ፖለቲካ ጉዳዮች ምርምር ክፍል ሃላፊ
አቶ አበበ አይነቴ እንደሚሉት፥ መንግስት በፖለቲካ አባልነት እና በብሄር ተዋጽኦ ሽፋን የሚደረገውን ስልጣንን ያለ
አግባብ የመጠቀም ችግር ተገንዝቦ ችግሩን እፈታዋለሁ ማለቱ የችግሩ መፍትሄ መጀመሪያ ነው።

የሶስተኛ ዲግሪ እጩ የሆኑት አቶ ሙሉቀን ሀብቱ በበኩላቸው፥ እውነተኛ ለውጥን ያለመ መንግስት ጥገናዊ ለውጥን
ሳይሆን ስር ነቀል የሚያመጣ መታደስን ያድርግ የሚል ሃሳብ አላቸው።

ቃል በመግባት አደርገዋለሁ ማለት ብቻ ሳይሆን፥ ትክክለኛ ምላሽ መስጠት እንዳለበት በመጥቀስ።

የመታደስ ጅማሮው ስልጣንን የግል ጥቅም ማስፈፀሚያ ያደረጉ ሹመኞችን በማንሳት የሚቆም ሳይሆን፥ ህዝቡ
ያነሳቸውን ጥያቄዎች የሚመልስ መሆን አለበት የሚለውም የምሁራኑ ሃሳብ ነው።

አቶ ሙሉቀን መንግስት የህዝብ ጥያቄ የሆኑትን የፍትህ እና የመልካም አስተዳደር እጦት ጥያቄዎችን ለመመለስ
እና ለማረጋገጥ መስራት እንዳለበት ይገልጻሉ።

መንግስት አደርገዋለሁ የሚለው ለውጥ መሰረታዊ ግቡ የህዝብን ፍላጎት የሚያሟላ አመራርን ማምጣት መሆን
አለበት የሚሉት አቶ አበበ ደግሞ፥ አሁን ቃል መግቢያ ሳይሆን የተግባር ወቅት በመሆኑ መሬት የወረደ የተግባር
ለውጥ ያሻል ነው ያሉት።

ተግባራዊ እርምጃው አመራሩን ከአንዱ ወደ ሌላ ቦታ ማዛወር ሳይሆን፥ ህዝቡን አዳምጦ ምላሽ የሚሰጥ አመራር
በክህሎት እና እውቀት መዝኖ የሚገባውን ስፍራ ማስቀመጥ መሆን አለበት የሚል ሃሳብም በምሁራኑ ተነስቷል።

አዲስ ካቢኔ ማዋቀርን የችግሮች ሁሉ መፍቻ አድርጎ ማሰብ ተገቢ አይደለም የሚሉት አቶ ሙሉ ቀን፥ መንግስት
የካቢኔ ሹም ሽር ማድረግን ለጥያቄ ምላሽ መስጫ መንገድ አድርጎ መመልከት እንደሌለበትም ተናግረዋል።

ከዚያ ይልቅ ዘላቂ ተቋማዊ የአሰራር ስርዓትን መዘርጋት እና የማያሰሩ ስልቶችን መለወጥ ለዘላቂ መፍትሄው
አስፈላጊ መሆኑን ያስረዳሉ።

ምሁራኑ ተቋማትን በተዘረጋ ስርዓት በመምራት መንግስት ቀጣይነት ያለው ሂደት ማድረግ መቻል እንዳለበትም
አንስተዋል።
admin@hebrezema.info
1