1
    HEBREZEMA.INFO
    INDEPENDENT NEWS & MEDIA
    DESIGNED BY ZEWDU TEKLU
    © COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED 2007.
የቤተክርስቲያኗ አመራሮች ምዕመኑን በማስተማር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ
ማትያስ አሳሰቡ
October 23, 2016
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ)
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን
በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ከመንፈሳዊ ተግባራት
ጐን ለጐን ስለ ሰላም፣ ፍቅርና የሀገር ዕድገት
ምዕመኑን በማስተማር ረገድ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት
እንዲወጡ ፓትሪያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ
አሳሰቡ።

ቤተክርስቲያኗ ሰላም ለማስፈን በሚደረገው እንቅስቃሴ
ተሳትፎዋን በማሳደግ ለሕዝብና ለአገር ደህንነት
እንደምትሰራ አስታውቃለች።

የቤተ ክርስቲያኗ ዓመታዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ዛሬ
ተጀምሯል።

በዚህ ወቅት ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ
እንዳሉት ቤተ-ክርስቲያን ሰላም ለማስፈን በሚደረገው
እንቅስቃሴ የበለጠ መስራት ይኖርባታል።
በተለይም ዘርን በመለየት፣ የአገርን አንድነት በመፈታተንና በኃይማኖት ምክንያት የሚነሱ እንቅስቃሴዎች ሕዝቡንና
የአገሪቱን ኃይማኖቶች የሚጎዱ በመሆናቸው ምእመኑ ጥንቃቄ እንዲያደርግ በትኩረት ማስተማር ይገባናል ነው ያሉት፡፡

የኃይማኖት አባቶች የሕዝብን አንድነት የሚያስጠብቁ፣ እርስ በእርስ የሚያስማሙና የሚያግባቡ ትምህርቶችን
እንዲያስፋፉም መክረዋል።

"የኃይማኖት አባቶች ለምእመኑ ማስተማር ያለባቸው ሰላምን የሚሰብከውን ምንም ያልተቀላቀለበትን የፈጣሪ ቃል
ሊሆን ይገባል'' ብለዋል፡፡

''የፈጣሪ ቃል ሁሉንም ያስማማል፣ ሁሉንም ያግባባል በመስማማት ላይ የተመሰረተ የአንድነትና የሰላም ፍሬን
ለማፍራት ያስችላል'' ነው ያሉት፡፡

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተከሰቱ ግጭቶችና ሁከቶች ተፈቃቅረውና ተዋደው ለዘመናት በአንድነት የኖሩትን ሕዝቦች
እርስ በእርስ እንዲቃቃሩ ሲያደርግ እንደሚስተዋልም ጠቁመዋል፡፡

እንደ ፓትሪያርኩ ገለጻ "በተፈጠረው ግጭት የሰው ህይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፣ በርካቶች ያለስራ ቀርተዋል፣
በሕዝቦች መካከልም የሕሊና ስብራት ተፈጥሯል"።

በዚህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን በተፈጠረው ክስተት ጥልቅ ሀዘን ተሰምቷታል ነው ያሉት።

ሰላሙ አስተማማኝ እስኪሆን አባቶች ሰፊ ስራ እንደሚጠበቅባቸው ያመለከቱት አቡነ ማትያስ፥ ጉባኤው በሰላም፣
በልማት ሥራ መስፋፋትና በስብከተ ወንጌል መጠናከር ላይ ተወያይቶ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ መናገራቸውን ኢዜአ
ዘግቧል።
admin@hebrezema.info
1