1
    HEBREZEMA.INFO
    INDEPENDENT NEWS & MEDIA
    DESIGNED BY ZEWDU TEKLU
    © COPYRIGHT. ALL RIGHTS RESERVED 2007.
የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር አገልግሎት ወደ ደረቅ ወደቦች የሚገቡ እቃዎችን ማመላለስ ሊጀምር ነው
November 16, 2016
አዲስ አበባ፣ ህዳር 7፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ)
በሙከራ ላይ ያለው የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር አገልግሎት
ከአራት ወራት በኋላ ወደ ደረቅ ወደቦች የሚገቡ
እቃዎችን ማመላለስ ይጀምራል።

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ
አገልግሎት ድርጅት ወደቦችን ከዋናው የባቡር መስመር
ጋር የሚያስተሳስሩ ሀዲዶች እየተገነቡ ነው ብሏል።

የድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አህመድ ቱሳ
እንደገለጹት፥ የሞጆ ደረቅ ወደብን ከባቡር መስመሩ ጋር
ለማገናኘት እየተሰራ ያለው 3 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር
ርዝመት ያለው ሀዲድ በቀጣዩ ሚያዝያ ወር ተጠናቆ ስራ
ይጀምራል።

በድርጅቱ የወደብ እና ተርሚናል ዘርፍ ምክትል ስራ
አስፈጻሚ አቶ ደሳለኝ ገብረህይወት በበኩላቸው፥ የደረቅ
ወደቦች ከባቡር ጋር መተሳሰር ከዚህ ቀደም ሲነሱ የነበሩ
ቅሬታዎችን እንደሚፈታና ከጅቡቲ ወደ ወደቦች
የሚገባውን እና የሚወጣውን እቃ በፍጥነት እና በብዛት ማድረስ ያስችላል ብለዋል።

የሞጆ ደረቅ ወደብ ለአዲስ አበባ ቅርብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከሌሎች ወደቦች በተለየ መልኩ በባለሀብቶች ዘንድ ተመራጭ ነው ያሉት የወደቡ ስራ አስኪያጅ
አቶ ታዬ ጫላ፥ ከባቡሩ ቀጥታ እቃዎችን ማራገፍ ሲጀምር በወደቡ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚነሱ ችግሮችን እንደሚያቃልል ገልፀዋል።

በተያያዘ የኮምቦልቻ እና መቀሌ ደረቅ ወደቦችም ተጨማሪ ወጪ ሳይወጣባቸው ከወዲሁ ከዋናው የባቡር መስመር ጋር እንዲተሳሰሩ ተደርጎ እየተገነቡ ነው።

ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁምም ወደቦቹ የባቡር ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል።

ደረቅ ወደቦች ከባቡር ጋር መተሳሰራቸው ጅቡቲ ላይ ከመርከብ ወደ መኪና ለመጫን ይወስድ የነበረውን ጊዜ በማስቀረት በቀጥታ በባቡር አማካኝነት እቃዎችን
ወደ ወደቦች ማድረስ ያስችላል።

ይህም ወጭን በመቀነስ የወጪ ገቢ ንግዱን ያቀላጥፋል ተብሎ ይጠበቃል።
admin@hebrezema.info
1